እርሻውን ተመልከቱ
“ እናንተ ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ ” ዮሐንስ 4፡35
በከተማችን በአካባቢያችን ወንጌል እንደሚገባ እንዲሰበክ ሰዎች ከጥፋት እንዲመለሱ ከዘላለም ሞት እንዲድኑ ከመቼውም ግዜ በበለጠ ልናስብበት የሚገባ ግዜ አሁን ነው ዛሬ ዓለማችንን ስንመለከት ግዜው ምን ያህል ተሰባሪ እና በፍጥነት ተለዋዋጭ እንደሆነ አስተማማኝ እንዳልሆነ መረዳት ለማንም አዳጋች አይደለም ከዳንበት ካመንበት ቀን ይልቅ የጌታ መምጣት የቀረበበት ወቅት ለመሆኑ አጠራጣሪ ነገር አይደለም ስለዚህ የጌታን አዳኝነት ገብቶን የተቀበልን ጌታን በግል ህይወታቸው ለማየያውቁት ለጠፉት ነፍሳት ግድ እንዲለን የጌታን የማዳን ወንጌል እንድንናገር እግዚአብሔር በቃሉ ያሳስበናል:: “ ... የቀደመውንም ሥራህን አድርግ `` ራዕይ 2፡5
ለነፍሳት መዳን ለመመስከር እና ለመፀለይ ምንም ዓይነት ቀጠሮ አያስፈልግም በልዩ ልዩ ምክንያት መመስከር እና መፀለይ ያቋረጥንም ካለን ካቆምንበት መጀመር እንችላለን የመፀለያዉ ጊዜ የመመስከሪያው ግዜ አሁን እንደሆነ መፅሐፍ ቅዱስ ይነግረናል “ እናንተ ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ ” ዮሐንስ 4፡35
በመመስከር እና በምልጃ ዉጤት እንድናይ አስቀድሞ ከራሳችን ህይወት በመጀመር ቸልተኝነታችንና ስንፍናችንን ልንናዘዝና ንሰሃ ልንገባ ያስፈልገናል ክርስቶስ የሞተለትን ዋና ዓላማ የሰው ዘርን መዳን ጉዳይ ቸል ያልን ግዴለሽ የሆንን ይህ በራሱ ንስሃ ያስፈልገዋል እግዚአብሔር በሚጠፉ ሕዝቦችና በራሱ መሃል የሚቆሙና የሚማልዱ ሰዎችን ይፈልጋልና
( ሕዝ 22፡30 )
ዛሬ በትምህርት ቤታችን፤ በቤታችን፣ በአካባቢያችን፣ በስራ ቦታችን፤ እንዲሁም በከተማችን እጅግ ብዙ ወገኖቻችን ደህንነትን አላገኙም በዘላለማዊ ሞት ፍርድ ስር ነው የሚኖሩት እነርሱን ከፍርድ ለማዳን በነርሱና በእግዚአብሔር መሃል ልንቆምና ስለ ደህንነታቸው ልንማልድ ባገኝነው አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም የደህንነትን መንገድ ልናሳያቸው ልንነግራቸው ያስፈልጋል ፡፡ ነፍሳት መዳን የሚችሉት ቤተ ክርስቲያን የጌታን በጎነት ስትመሰክር እና በፀሎት፣ በምልጃ በመቃተት በእግዚአብሔር ፊት መቅረብ ስትችል ነዉ!
በቃሉ ጉልበት የጠላት ክንድ ይዝላል የጨለማው ብርታት ይሰበራል ምክንያቱም በፀሎት የእግዚአብሔር ሀይልና ምህረት ይለቀቃል የተለቀቀ የእግዚአብሔር ሀይልና ምህረት ደግሞ ለወንጌል ሥርጭት እንቅፈት የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ያስወግዳል በተጨማሪም ሰዎች ወንጌል እንዲቀበሉ ልባቸውን ያዘጋጃል።
ስለዚህ እኛ ለነፍሳት መዳን የምናደርገው የምልጃ ፀሎት እና ምስክርነት በምንኖርበት አካባቢ ሁሉ ልዩነትን ያመጣል ስለዚህም ክርስቲያን ወንድሞች ሆይ በርትተን የጌታን ሥራ እንሠራ ዘንድ ጌዜው አሁን ነውና ለብዙዎች መዳን በፀሎት እና በምልጃ፤ በምስክርነት እንጋደል ዘንድ ይጠበቅብናል ! ለዚህም ጌታ ይርዳን!