>> Amharic Page
  • New Post 1
  • New Post 2
  • New Post 3
  • New Post 4
  • Link 1
  • Link 2
  • Link 3
  • Link 4

Articles

  • 1
  • |
  • 2

ውጊያ ከውስጥ ወደ ውጭ

‹‹…..ስለዚህ ክፉ መሻቱን ትፈፅሙ ዘንድ በሟች ስጋችሁ ላይ ሃጢአት እንዲነግስበት አታድርጉ፡፡ ብልቶቻችሁን የሃጢአት መሳሪያ አድርጋችሁ ለሃጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የፅድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ፡፡ ከፀጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆናችሁ፤ ሃጢአት አይገዛችሁምና “ ሮሜ 6፡1-14


በዚህ ዘመን፤ ብዙዎቻችን በክርስትና ሕይወታችን ስለሚሆን መንፈሳዊ ውጊያ ስናስብ በአብዛኛው ከባላጋራችን ዲያብሎስ ስለሚላክብን ፍላፃ እና እኛም በክርስቶስ ባገኘነው የጦር ዕቃ ጦር መሠረት የምንዋጋውን ጦርነት ነው፡፡ ይህን ውጊያ ፤ ክርስቶስ ኢየሱስ ዲያብሎስን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመስቀል ላይ ሥራው በማሸነፉ ፤ ለማሸነፍ የምናደርገው ጦርነት ሳይሆን፤ የተሸነፈው ጠላታችን ዲያብሎስ ዘወትር እንደሚያገሳ አንበሳ ዙሪያችንን ይዞራልና ተግተን ልንዋጋ ስለሚገባ ነው፡፡ ሆኖም ግን፤ ከዚህ ጦርነት ጎን ለጎን፤ እንዳውም በቅድሚያ በሕይወታችን የምናስተናግደው ጦርነት እንዳለ ከላይ በተጠቀሰው ክፍል ሐዋርያው ጳውሎስ ይናገራል፡፡ ይህ የተገለፀው ውጊያ አዲስ በዳነ ክርስቲያንም ሆነ በጌታ ቤት በቆየች ነፍስ ውስጥ ሁሌም ቢሆን ያለ ጦርነት ሲሆን፤ የጦር አውድማውም የሰው ልጅ አካል እንደሆነ እናነባለን፡፡


አጠር ባለ መልኩ ስንቃኘው፤ ይህ ጦርነት ፅድቅ እና ኃጢአት በሰው ልጅ ልቡና ላይ ለመንገስ የሚያደርጉት ትግል ሲሆን፤ በውጊያው አሸናፊ ለመሆን ደግሞ ሁለቱም ባላንጣዎች የሰውነት ክፍሎቻችንን /ብልቶቻችንን/ እንደ ጦር መሳሪያ እቃ አድርገው ለመጠቀም እንደሚታገሉ እንረዳለን፡፡ በመሆኑም በዚህ ፅሁፍ መግቢያ ላይ በተጠቀሰው ከዲያብሎስ ጋር ባለን ውጊያ ድል አድራጊዎች ለመሆን በቅድሚያ በውስጣችን ባለው ውጊያ አሸናፊዎች መሆን ይኖርብናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በክርስቶስ የዳነ ሰው ከኃጢአት ጋር ምን ያህል እንደተራራቀ አድርጎ ሊያስብ እንደሚገባው ሲያትት በሚከተለው መልክ አቅርቦታል፡፡

“ ሁለት በተጋቡ ሰዎች መካከል የትዳር ሕግ የሚሰራው በሕይወት እስካሉ ድረስ ብቻ እንደሆነ ሁላችን እናውቃለን፡፡ ከባል እና ከሚስት መካከል አንዱ ቢሞት በሕይወት በቀረው ላይ ሕጉ እንደማይሰራና ሌላ ለማግባትም ደረጃ ድረስ በሕግ የተፈቀደ ነው፡፡ የእኛም አሮጌ ማንነታችን ክርስቶስ ጋር በመስቀል ላይ በተሰቀለ ሰዓት ለሕግ የሞትን ስንሆን፤ አዲሱ ከክርስቶስ ጋር ከሞት የተነሳው ሰውነታችን ግን ለክርስቶስ የሚኖር እንደሆነ ልናስተውል ይገባናል፡፡ ስለዚህም ጸጋ እንጂ ሕግ የበላይ አይደለም “

በዚህም በአዲሱ ሰውነታችን ከክርስቶስ ጋር ያለን መንፈሳዊ ሕብረት እና አንድነት የተጠበቀ እንዲሆን በየእለት-ተእለት ሕይወታችን በነቃ /active/ በሆነ ማንነት ልናደርጋቸው የሚገቡትን ነገሮች እንደሚከተለው ተቀምጠዋል፡-

-ለኃጢአት እንደሞታችሁ ፤ ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ህያዋን እንደሆናችሁ ቁጠሩ፡፡

(ሮሜ 6፡11)

-ክፉ መሻቱን ትፈፅሙ ዘንድ በሟች ስጋችሁ ላይ ሃጢአት እንዲነግስበት አታድርጉ፡፡ (ሮሜ 6፡12)

-ብልቶቻችሁን የክፋት መሳሪያ አድርጋችሁ ለሃጢአት አታቅርቡ፡፡ (ሮሜ 6፡13)

-ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሸገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፡፡

(ሮሜ 6፡13)

-ብልቶቻችሁንም የፅድቅ መሳሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ፡፡ (ሮሜ 6፡13)

እነዚህን ነጥቦች ተኮር ብለን ስንመለከታቸው ከሃጢአት ጋር ባለን ግብግብ ድል ነሺነት የሚጀምረው በቅድሚያ ራሳችንን በክርስቶስ ኢየሱስ ዳግም የተወለድን ህያዋን እንደሆንን በመቁጠር ነው፡፡ ይህንን እውነት አምነን በመቀበል፤ በውስጣችን በሚያፀናልን በመንፈስ ቅዱስም አማካኝነት በመታገዝ፤ ቀጣዩ ሂደት ሃጢአት በሟች ስጋችን ላይ እንዳይነግስ ማድረግ የሚገቡን ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህን እርምጃዎች ስንመለከታቸው ሀዋርያው ጳውሎስ አቅርቡ እና አታቅርቡ በሚሉ ሁለት ተቃራኒ ቃላቶች ቋጭቶታል፡፡ አታቅርቡ በሚልበት ክፍል፤ ጌታ ኢየሱስ በፅድቁ በአካል ክፍሎቻችን ሁሉ ላይ ለመሰልጠን እንደሚመኝ ሁሉ ጠላትም በሃጢአት እና በእርኩሰት ሊሰለጥንባቸው ይመኛልና ለጠላት ብልቶቻችን የሃጢአት መጠቀሚያ አድርገን እንዳናቀርብ የገለፀው ነው፡፡ አቅርቡ ሲል ደግሞ የሰውነት ክፍሎቻችንን በሙሉ የፅድቅ መሰልጠኛ እንዲሆኑ ለጌታ ለማቅረብ እንድንተጋ ሲነግረን ነው፡፡ ይህን እንድናደርግ በሚነግረን ሰዓት፤ ክርስቶስን ከሰይጣንና ከክፋቱ ጎን በተቃርኖ የቆመ የሰው ልጆችን ለመቆጣጠር የሚተጋ ተወዳዳሪ አድርገን ብቻ እንዳንስለው እሰጋለሁ፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ እኛን የራሱ ለማድረግ ራሱን አሳልፎ የሰጠ እናም በክቡር ደሙ የገዛን ልጆቹ ነን፤ እንዳውም ጠላታችን ዲያብሎስ ነው ዋጋ የተከፈለልንን እኛን በተንኮሉና በኃጢአት በማባበል ከክርስቶስ እጅ ለማውጣት የሚተጋው፡፡ በመሆኑም ክርስቶስ የራሱ ቢያደርገን፤ ፅድቁን በሕይወታችን ሊገልጥ ቢመርጠን ይገባዋል፤ ምክንያቱም በዋጋ ገዝቶናልና፡፡

በሃጢአት ላይ በምናምፅበት ጊዜ ደግሞ ሊያግዘን የእግዚአብሔር ጸጋ ከእኛ ጋር ነው፤ ምክንያቱም ሮሜ 6፡14 ‹‹በሕግ በታች ሳትሆኑ ከጸጋ በታች ናችሁ ›› ይላልና፡፡ ሕግ በተፈጥሮው ልክ የሆነውንና ያልሆነውን ለመለየት ከመጥቀም እናም የጸጋ ዘመን እስኪመጣ ድረስ እንደሞግዚት ከማገልገል ያለፈ ጠቀሜታ የለውም፡፡ ጸጋ ግን ልክ ያልሆነ ነገር /ኃጢአት/ እንዳይሰራ የሚያስችል ሃይል ያለው ላልተገባን ለእኛ የተሰጠ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡

ስለዚህም ክርስቲያን ወንድሞች በየዕለት ኑሮአችን በስጋችን ላይ ኃጢአት እንዳይነግስ፤ ብልቶቻችንን ሁሉ የፅድቅ መገለጫዎች እንዲሆኑ ለእግዚአብሔር በማቅረብ በአካላችን ላይ ለሃጢአት እንዳይነግሥ አሻፈረኝ በማለት በኃጢያት ላይ እንድናምፅ /revolt/ ይገባናል !!


  • Bible lookup
  • Bible Dictionary
  • Bible Studay Materials
  • Vision
  • Statement of Faith
  • Mission
  • Bible Study
  • Young Adult
  • Youth
  • Sunday School
  • Holistic
  • Pastoral
  • Choir
  • Sisters
  • Brothers
  • Deacon
  • Elders
  • Prayer
  • Litrature & Drama
  • Multimedia
  • Usher
  • Worship Lead
  • Library
  • Upcoming Events
  • Calendar
  • Video_Audio
  • Photo Gallery

© Copyright 2011 Ethiopian Evangelical Church, Ottawa, Canada